languageIcon
search
search
brightness_1 ንጹሕ ሆኖ ዱዓእ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

አቡ ሙሳ አል-አሽዐሪይ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ነቢዩ -የአላህ እዝነተና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ወደአውጣስ ጦር ሲልኳቸው ከአጎታቸው ከአቢ ዓሚር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ጋር የነበራቸውን ታሪክ እንዳስተላለፉት አቢ ዓሚር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ተገደሉ፡፡ ከመሞታቸው በፊት ለነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሰላምታ እንዲያደርሱላቸውና ዱዓእ እንዲያደርጉላቸው አቢ ሙሳ አል-አሽዐሪይን አደራ አሏቸው፡፡ አቡ ሙሳም     -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹የኛንና የአቢ ዓሚርን ዜና ነገርኳቸው፡፡ ‹‹አላህ ወንጀሎቼን እንዲምርልኝ እንዲጠይቁልኝ ንገራቸው፡፡›› ብሎኛል ብዬ ነገርኳቸው፡፡ የአላህ መልእክተኛም ውሃ እንዲመጣላቸው አደረጉ፡፡ ከውሃውም ዉዱእ አደረጉ፡፡ ከዚያ የብብታቸውን ንጣት እስከማይ ድረስ እጆቻቸውን አነሱና፣ “አላህ ሆይ! ለዑበይድ ወንጀሎቹን ማርለት፡፡ ለዓሚር አባት፡፡” አሉ፡፡ አያይዘውም፣ “አላህ ሆይ! በትንሳኤ እለት ከበርካታ ፍጡራንህ በላይ አድርገው፡፡” አሉ፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (4323)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (2498) ላይ ዘግበውታል፡፡

brightness_1 ወደቂብላህ አቅጣጫ መዞር

ዐብዱላህ ኢብን ዐብባስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት፣ ‹‹ዑመር ኢብን አል-ኸጣብ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዲህ አሉኝ፣ ‹‹በበድር ጦርነት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላማታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ወደአጋሪያን ተመለከቱ፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሰሐቦቻቸው ደግሞ ሶስት መቶ አስራ ዘጠኝ ናቸው፡፡ የአላህ ነቢይ ወደቂብላ ዞሩ፣ ከዚያም እጆቻቸውን አንስተው፣ “አላህ ሆይ! ቃል የገባህልኝን ፈጽምልኝ፡፡ አላህ ሆይ! ቃል የገባህልኝን ስጠኝ፡፡ አላህ ሆይ! ከኢስላም የሆኑ እነዚህ ቁጥራቸው ጥቂት የሆነ ታጋዮች ቢጠፉ በምድር ላይ አትመለክም፡፡” በማለት ጌታቸውን ተለማመጡ፡፡ እጆቻቸውን አንስተው፣ ወደቂብላህ ዞረው ከትከሻቸው ላይ ያለው ጭርቃቸው እስኪወድቅና አቡ በክር ከእሳቸው ጋር በመሆን ‹‹የአላህ ነቢይ ሆይ! ጌታህን መጠየቅህ ይብቃህ፡፡ እሱ ቃል የገባልዎን ይፈጽምልዎታል፡፡…›› እሰከሚሏቸው ድረስ ጌታቸውን ከመማጸን አልታከቱም፡፡›› ብለዋል፡፡ ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1763) ላይ ዘግበውታል፡፡       

brightness_1 ደዓእን መደጋገምና በእሱም ላይ መለማመጥ

በዚህ ላይ ከዚህ በላይ ያሳለፍነው የኢብን ዐብባስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ሐዲሥ ማስረጃ ይሆናል፡፡ በዚህ ሐዲሥ ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አልላሁምመ አንጂዝ ሊ ማ ወዐድተኒ፣ አልላሁምመ ኣቲ ማ ወዐድተኒ፡፡ /አላህ ሆይ! ቃል የገባህልኝ ፈጽምልኝ፡፡ አላህ ሆይ! ቃል የገባህልኝን ስጠኝ፡፡” ሲሉ ከትከሻቸው ላይ ያለው ጭርቃቸው እስኪወድቅና አቡ በክር ከእሳቸው ጋር በመሆን ‹‹የአላህ ነቢይ ሆይ! ጌታህን መጠየቅህ ይብቃህ፡፡›› እሰከሚሏቸው ድረስ ጌታቸውን ከመማጸን አልታከቱም ብለዋል፡፡  ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1763) ላይ ዘግበውታል፡፡  

እንደዚሁ ቡኻሪና ሙስሊም ከአቢ -ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በዘገቡት ሐዲሥ ላይ ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ለዱሥ ጎሣ  ባደረጉት ዱዓእ ላይ፣ “አላህ ሆይ! የዱስ ጎሳዎችን ቀጥተኛውን መንገድ ምራቸው፡፡ አምጣቸውም፡፡አላህ ሆይ! የዱስ ጎሳዎችን ቀጥተኛውን መንገድ ምራቸው፡፡ አምጣቸውም፡፡” ብለዋል፡፡ ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2937)፣ ሙስሊም በቁጥር (2524) ላይ ዘግበውታል፡፡    

እንደዚሁ በሙስሊ ትክክለኛ የሐዲሥ ዘገባ፣ “ጉዞ በሚያሰረዝም፣ ፀጉሩ የተቆጣጠረና አቧራ የለበሰ ሆኖ እጁን ወደሰማይ ዘርግቶ ጌታዬ! ጌታዬ!   ይላል፡፡” የሚል ተዘግቧል፡፡ ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1015) ላይ የዘገቡት ሲሆን ይህ በመደጋገም መለመን ነው፡፡

ነቢያዊ ፈለጉ ሶስት ሶስት ጊዜ ዱዓእ  ማድረጉ  ነው፡፡ ኢብን መስዑድ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ባስተላለፉትና ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሐዲሥ፣ ‹‹ዱዓእ ሲያደርጉ ሶስት ሶስት ጊዜ ያደርጉ ነበር፡፡ ከጠየቁም ሶስት ሶስት ጊዜ ይጠይቁ ነበር፡፡ ካሉ በኋላ ሶስት ሶስት ጊዜ፣ “አልላሁምመ ዐለይከ ቢቁረይሽ፡፡ /አላህ ሆይ! በቁረይሽ ላይ ይሁንብህ፡፡/” አሉ፡፡›› የሚል ይገኝበታል፡፡ ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (240)፣ ሙስሊም በቁጥር (1794) ላይ ዘግበውታል፡፡ 

 

brightness_1 ዱዓዬ ውስጥ ምንድን ነው የምለው?

ፋይዳ፡- ምናልባት አንዳንድ ሰዎች፤ ዱዓዬ ውስጥ ምንድን ነው የምለው? ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡

መልሱ፡- ምድራዊውንም ሆነ የወዲያኛው ዓለም ጉዳዮችን ጠይቁ፡፡ ጥቅል ይዘት ባላቸው ቃላት በዱዓችሁ ውስጥ ተበራቱ፡፡ እነዚህ ዱዓዎች በቁርአንና በሐዲሥ ላይ የተጠቀሱ ናቸው፡፡ በውስጣቸው ለምድራዊውም ሆነ ለወዲያኛው ዓለም ጠቃሚ የሆኑ ዱዐዎች አሏቸው፡፡ ለነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- የቀረበውን ይህን ጥያቄ እስኪ አስተውሉ፡፡ ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ለአንድ ሰው በምድራዊውና በወደያኛው ዓለም ሊጠቅሙት በሚችሉ ታላቅ የሆኑ ቃላት ነበር ምላሻቸውን የሰጡት፡፡ እነዚህ ቃላት ምነኛ የላቁ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ታዲያ እናንተም አጥብቃችሁ ልትይዟቸውና ልታስተነትኗቸው ይገባል፡፡

አቢ ማሊክ አል-አሽጀዒይ ከአባታቸው -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት፣ ‹‹ አንድ ሰው ወደየአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- መጣና፡- ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አላህን ስጠይቅ ምን ልበል?› በማለት ሲጠይቃቸው እሳቸውም፣ “አልላሁምመ ኢግፊር ሊ ወርሐምኒ ወህዲኒ ወዓፊኒ ወርዙቅኒ፡፡ /አላህ ሆይ! ወንጀሌን ማርልኝ፣ እዘንልኝ፣ ቀጥተኛውን መንገድ ምራኝ፣ ይቅር በለኝ፣ ሲሳይም ስሰጠኝ፡፡/ አሉና ከአውራ ጣታቸው በስተቀር ሌሎች ጣቶቻቸውን ሰበሰቡና፣ “እነዚህ ቃላት በምድራዊ ሕይወትህና በወዲያኛው ዓለም ሕይወትህ የሚጠቅሙህን ነገሮችን ሁሉ በእርግጥ ይሰበስቡልሃል፡፡” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡ ሙስሊም ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2697) ላይ  ዘግበውታል፡፡

እሳቸው ባስተላለፉት ሌላ ዘገባ ደግሞ፣ ‹‹አንድ ሰው ኢስላምን ከተቀበለ ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሰላትን ያስትምሩት ነበር፡፡ ከዚያም በእነዚህ ቃላት ዱዓእ እንዲያደርግ ያዙታል፣ “አልላሁምመ ኢግፊር ሊ ወርሐምኒ ወህዲኒ ወዓፊኒ ወርዙቅኒ፡፡ /አላህ ሆይ! ወንጀሌን ማርልኝ፣ እዘንልኝ፣ ቀጥተኛውን መንገድ ምራኝ፣ ይቅር በለኝ፣ ሲሳይም ስሰጠኝ፡፡/” ሙስሊም ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2697) ላይ ዘግበውታል፡፡