brightness_1
በምግቡ መጀመሪያ ላይ የአላህን ስም ማውሳት
ዑመር ኢብን አቢ ሰለመህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹በአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ቤት ውስጥ ልጅ ነበርኩኝ፡፡ እጄ መመገቢያ ትሪውን ይነካካ ነበር፡፡ እንዲህ አሉኝ፣ “አንተ ልጅ ሆይ! የአላህን ስም አውሳ፡፡ በቀኝህም ተመገብ፡፡ ከፊት ለፊትህም ተመገብ፡፡” ከዚያች ጊዜ አንስቶ አመጋገቤ እንደዚያ ከመሆን አልተወገድም፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (5376)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (2022) ላይ ዘግበውታል፡፡
ለአንድ ሙስሊም የተሻለው የአላህን ስም ማውሳትን አለመተዉ ነው፡፡ የአላህን ስም ማውሳቱን ከረሳና ካስታወሰ፣ ‹ቢስሚልላህ አውወለሁ ወኣኺረሁ፡፡ በመጀመሪያውም በመጨረሻው ላይ በአላህ ስም፡፡/› ማለቱ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡
ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- “አንዳችሁ ሲመገብ የአላህን ስም ያውሳ፡፡ የአላህን ስም በመጀመሪያው ላይ ማውሳትን ከረሳ ቢስሚልላህ አውወለሁ ወኣኺረሁ፡፡ በመጀመሪያውም በመጨረሻው ላይ በአላህ ስም፡፡/ ይበል፡፡” ማለታቸውን የዘገቡበት ሐዲሥ ነው፡፡ ሐዲሡን አቢ ዳዉድ በቁጥር (3767)፣ አት-ቲርሚዚይ በቁጥር (1858) የዘገቡት ሲሆን አል-አልባኒይ ትክክለኛነቱን አረጋግጠዋል፡፡ ሰሒሑ-ልጃሚዕ ቅጽ ፡ 1 ገጽ፡ 282፡፡
ሐዲሡ አንድ ሲመገብ ከሸይጣን ጋር እንዳይመሳሰል በቀኝ እጁ መመገብ እንዳለበት አረጋግጧል፡፡ አንድ ሙስሊም ሲመገብ የአላህ ስምን ካላወሳ በምግቡ ላይ ሸይጣን ይጋራዋል፡፡ በግራ እጁ ከተመገበ ወይም ከጠጣ በዚህ ድርጊቱ ሸይጣንን ተመሳስሏል፡፡ ምክንያቱም ሸይጣን የሚመገበውም የሚጠጣውም በግራው ስለሆነ ነው፡፡
ሸይጣን ወደአንድ ቤት ውስጥ የመግባት፣ በውስጡም የማደርና ከቤቱ ቤተሰቦች ጋር ምግብን የመጋራት ከፍተኛ ጉጉት አለው፡፡ ጃቢር ኢብን ዐብዱላህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንድ ሰው ወደቤቱ ሲገባ በምግባቱና በምግቡ ላይ የአላህን ስም ካወሳ ሸይጣን፡- ማደሪያና እራት የላችሁም ይላል፡፡ ሰውዬው ሲገባ በመግባቱ ላይ የአላህን ስም ካላወሳ ሸይጣን፡- ማደሪያ አገኛችሁ፡፡ ” በምግቡ ላይ የአላህን ስም ካላወሳ ሸይጣን፡- ማደሪያና እራት አገኛችሁ፡፡ ይላል፡፡” ሲሉ መስማታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሐዲሡን ሙስሊም በሐዲሥ ቁጥር (2018) ላይ ዘግበውታል፡፡