languageIcon
search
search
brightness_1 የሌሊት ሰላትን በላጭ በሆነው ወቅት መስገድ ከነቢያዊ ፈለጎች መካከል አንዱ ነው፡፡

በውሰጡ የነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ተግባረት የሆኑ በርካታ ፈለጎችን አካቷል፡፡

የሌሊት ሰላትን በላጭ በሆነው ወቅት መስገድ ከነቢያዊ ፈለጎች መካከል አንዱ ነው፡፡

‹‹በላጩ የሌሊት ሰላት ወቅት የትኛው ነው?›› ከተባለ፡-

ምላሹ፡- እንደሚታወቀው የዊትር ሰላት ወቅት ከዒሻእ ሰላት በኋላ ጀምሮ ጎሕ እስከሚቀድ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ የዊተር ሰላት ወቅት በዒሻእና በፈጅር  ሰላት መካከል ነው፡፡

ይህን  የሚያመለክተው ማስረጃ፡-

ሀ. ከዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተላለፈው እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁን- የዒሻእን ሰላት በማጠናቀቃቸውና እስከፈጅር ሰላት ድረስ ባለው ጊዜ መካከል አስራ አንድ ረከዐዎችን ይሰግዱ ነበር፡፡ በየሁለቱ ረከዐዎችም ያሰላምታሉ፡፡ በአንድ ረከዐህም ዊትር ያደርጋሉ፡፡›› ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2031) ሙስሊምመ ደግሞ በቁጥር (736) የዘገቡት ሲሆን ሁለቱም ተስማምተውበታል፡፡

- የሌሊት ሰላት ወቅት ደግሞ ከእኩለ-ሌሊት በኋላ ያለው የሌሊቱ ሲሶ (አንድ ሶስተኛው) ክፍል ነው፡፡

ይህም ማለት ማንኛውም ሰው ሌሊቱን ለተለያዩ ክፍሎች ይከፍለዋል፡፡ ከዚያ ከሁለተኛው አጋማሽ በኋላ ባለው የሌሊቱ ሲሶ ክፍል ተነስቶ ይሰግዳል፣ ከዚያም በሌሊቱ የመጨረሻ ክፍል ይተኛል፡፡ ወይም ደግሞ የሌሊቱን የአራተኛና የአምስተኛ አንድ ስድሰተኛ የሌሊት ክፍል ቆሞ ሲሰግድ የስድስተኛ አንድ ስድስተኛ ክፍል ደግሞ ይተኛል፡፡ 

ይህንም የሚያረዳ ማስረጃ ደግሞ ከዐብሁላህ ኢብን ዑምር     -አላህ  መልካም ሥራዎቻቸውን ይቀበላቸው- የተላለፈው ሐዲሥ ሲሆን የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላየድ ይሁን- እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹በአላህ ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ጾም የዳዉድ -በእሳቸው ላይ ሰላም ይሁን- ጾም ነው፡፡ በአላህ ዘንድ ተወዳጁ ሰላት ደግሞ የዳዉድ ሰላት ነው፡፡ ግማሹን ሌሊት ይተኙ፤ ሲሶው ላይ ተነስተው ይሰግዱ፣ አንድ ስድስተኛውን ይተኙ ነበር፡፡ አንድ ቀን ይጾማሉ አንድም ቀን ያፈጥሩ ነበር፡፡›› ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (3420) ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (1159) ዘግበውታል፡፡

- አንድ ሰው ይህን ነቢያዊ ፈለግ ለመተግበር ከፈለገ የሌሊት ስሌቱ እንዴት ነው የሚሆነው?

ሌሊት የሚባለው ፀሐይ ከጠቀለችበት ጎሕ እስከሚቀድበት ጊዜ ድረስ እንደሆነ ያስባል፡፡ ከዚያ ይህን ጊዜ ለስድሰት ይከፋፍለዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ክፍልፋዮች የሌሊቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ሲሆን ከዚያ በኋላ በአራተኛው የሌሊቱ  አንድ ስድስተኛው ክፍልና በአምስተኛው የሌሊቱ አንድ ስድስተኛው ክፍል ተነስቶ ይሰግዳል፡፡ ይህ ደግሞ የሌሊቱ ሲሶ (አንድ ሶስተኛ) ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በመጨረሻው የስድስተኛው ክፍል  ይተኛል፡፡ ለዚህም ነው ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ፣ ‹‹ ‹‹እኔ ዘንድ ነቢየ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እኔ ዘንድ የተኙ ካልሆኑ በስተቀር አገኛቸው ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1133) ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (742) ዘግበውታል፡፡

በዚህ መንገድም በላጩ የሌሊት ሰላት ውስጥ ይሆናል፡፡ ይህም ከዚህ በላይ ባሳለፍነው የዐብዱላህ ኢብን ዐምር -አላህ ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደሰፈረው ነው፡፡

የርዕሱ ማጠቃለያ፡- የሌሊት ሰላት በላጭ ወቅት በሶስት ደረጃዎች ይመደባል፡፡ እነርሱም፡-

የመጀመሪያው ደረጃ፡- አንድ ሰው የሌሊቱን የመጀመሪያ አጋማሽ ከተኛ በኋላ ከዚያ በኋላ ከእንቅልፉ በመንቃት አንድ ሶስተኛውን ይሰግዳል፡፡ ከዚያ -ልክ እንዳሳለፍነው- አንድ ስድስተኛውን ይተኛል፡፡

ይህን የሚያመለክተው ማስረጃ፡- ከዚህ በላይ ያሳለፍነው የዐብዱላህ ኢብን ዐምር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ሐዲሥ ነው፡፡

ሁለተኛው ደረጃ፡- የመጨረሻውን የሌሊቱን የመጨረሻ አንድ ሶስተኛ ክፍል ከእንቅልፉ ነቅቶ ይሰግዳል፡፡

ይህን የሚያመለክተው ማስረጃ፡-

 አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹እጅግ የተባረከውና የላቀው ጌታችን የሌሊቱ የመጨረሻ ሲሶ ላይ ወደምድራዊው ሰማይ ይወርዳል፡፡ “ማነው የሚለምነኝ ልመናውን የምቀበለው፣ ማነው የሚጠቀኝ የሚጠይቀኝን የምሰጠው? ማነው ምህረት የሚጠይቀኝና ምህረት የማደርግለት?” ይላል፡፡›› ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1145) ሙሰሊም ደግሞ በቁጥር (758) ዘግበውታል፡፡ ከዚህ ሌላ ጃቢር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ያስተላለፉት ሐዲሥ ይገኛል፡፡ ይህን ሐዲሥ ወደፊት እንመለከተዋለን፡፡

ሶስተኛው ደረጃ፡- የመጨረሻውን ሌሊት እንደማይነሳ የፈራ  ሰው የመጀመሪያው ሌሊት ወይም የገራለትን የሊሊቱን ክፍል ይስገድ፡፡

ይህን የሚያመለከተው ማስረጃ፡-

ጁቢር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይወደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በመጨረሻው የሌሊ ክፍል መነሳትን የፈራ በመጀመሪያው ዊትር ይስገድ፡፡ የመጨረሻውን ለመነሳት የጓጓ በመጨረሻው ሌሊት ዊትር ያድርግ፡፡ በርግጥ የመጨረሻው ሌሊት -መላክት- የሚታደሙበት የሆነ ነው፡፡ ይህ በላጩ ነው፡፡›› ሙሰሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (758) ዘግበውታል፡፡

በዚህም የአላህ መልእክተኛ -የአላህ መልእክተኛ እዘነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ለአቢ ዘር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- የለገሷቸውና  አን-ነሳኢይ በአስ-ሱነኑ-ል-ኩብራ የሐዲሥ መድብል በቁጥር (2712) እንዲሁም አል-አልባኒይ በትክክለኛ የሐዲሥ ዘገባ መጽሐፋቸው በቁጥር (2166) የዘገቡት ምክር፣ ለአቢ ደርዳእ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይወደድላቸው- የለገሷቸውና አሕመድ በቁጥር (27481)፣ አቡ ዳዉድ በቁጥር (1433) እንዲሁም የአቢ ዳዉድ ትክክለኛ ሐዲሦች በማለት አል-አልባኒይ ባዘጋጁት መጽሐፍ ቅጽ ፡ 5 ገጽ ፡ 177 ምክር፣ ለአቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- የለገሷቸውና ሙሰሊም በቁጥር (737) በዘገቡት ምክር ሁሉም፣ ‹‹ወዳጄ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- በሶስት ነገሮች ላይ አደራ አሉኝ፡፡›› ካሉ በኋላ ከጠቀሷቸው አደራዎች መካከል፣ ‹‹ከመተኛቴ በፊት ዊትር እንድሰግድ›› የሚለው ይገኝበታል፡፡

brightness_1 አስራ አንድ ረከዐዎችን መስገድ

ይህ ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይወደድላቸው- ያስተላለፉት ሐዲሥ ይበልጥ ማስረጃ ነው፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነታና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ረመዳን ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ ከአስራ አንድ ረከዐዎች አይጨምሩም ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1147) እንዲሁም ሙስሊም በቁጥር (738) ዘግበውታል፡፡ 

የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- አስራ ሶስት ረከዐዎች መስገዳቸውን ከዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይወደድላቸው- ሐዲሥ ተላልፏል፡፡ 

አላህ ይበልጥ ዐዋቂ ነው በገሃድ የሚታየው ይህ ርዕስ የዊትርን የተለያየ ሁኔታ ያመለክታል፡፡ በአብዛኛው የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- የዊትር ሰላት አስራ አንድ ረከዐህ እንደነበርና አንዳንድ ጊዜም በአስራ ሶሰት ረከዐዎች ይሰግዱ ነበር፡፡ በዚህም ሁለቱን ከዚህ በላይ የሰፈሩ ሐዲሦችን በእንዲህ መልክ አንድ ልናደርጋቸው እንችላለን፡፡

brightness_1 ሐዲሥ ላይ በሰፈሩ ነቢዊ ፈለግ በሆኑ የሌሊት ሰላት መክፈቻዎች መጀመር -

ሀ. በሙስሊም ትክክለኛ የሐዲሥ ዘገባ ከዓኢሻህ --አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይወደድላቸው-- እንደተላለፈው፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሌሊት ላይ ለሰግዱ ከተነሱ ሰላታቸውን፣ “የጂብረል፣ የሚካኢልና የኢስራፊል ጌታ የሆንከው፣ ሰማያትና የምድር ፈጣሪ የሆንከው፣ ሩቁንም ቅርቡንም በእጅጉ ዐዋቂ የሆንከው አላህ ሆይ! በሕዝቦች መካከል ይለያዩበት በነበረው ነገር ላይ አንተ በእውነት ትፈርዳለህ፡፡ በፈቃድህ ከሚለያዩበት ጉዳይ ወደእውነተኛው ምራኝ፡፡ አንተ የምትሻውን ወደቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ ትመራለህ፡፡›› በሚለው ይጀምሩ ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ሙስሊም በቁጥር (770) ዘግበውታል፡፡

ለ. ቡኻሪና ሙስሊም ትክክለኛ በሆነ የሐዲሥ ዘገባ ከኢብን ዐብባስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ባስተላለፉት ሐዲሥ፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሌሊት ላይ ሲሰግዱ፣ “አላህ ሆይ! አንተ የሰማያትና የምድር ብርሃን ነህ፡፡ ምስጋናም ላንተ ነው፡፡ አንተ የሰማያትና የምድር አስተናባሪ ነህ፡፡ ምስጋናም ላንተ ነው፡፡ አንተ የሰማያት፣ የምድርና በውስጣቸውም ያሉ ነገሮች ሁሉ ጌታ ነህ፡፡ አንተ እውነት ነህ፡፡ ቃል-ኪዳንህም እውነት ነው፡፡ ንግግርህም እውነት ነው፡፡ መገናኘትህም እውነት ነው፡፡ ጁነትም እውነት ነው፡፡ ጀሀነምም እውነት ነው፡፡ ሰአቷም እውነት ነች፡፡ አላህ ሆይ! ላንተ እጅ ሰጠሁ፣ ባንተም አመንኩ፣ ባንተም ላይ ተመካሁ፣ ወዳንተም ተመለስኩ፣ ባምተም ተፋረድኩ፣ ወዳንተም ፍርድ ሰጠሁ፣ ያሳለፍኩትን ያዘገየኸሁትን፣ የደበቅኩትንም ሆነ ይፋ ያደረግኩትን ወንጀሌን ማርልኝ፡፡ አንተ አምላኬ ነህ፡፡ ካንተ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡” ይሉ ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡  ቡኻሪ በቁጥር (7499) ሙሰሊም ደግሞ በቁጥር (768) ሐዲሡን ዘግበውታል፡፡

 

brightness_1 በሐዲሥ የተዘገቡ ነቢያዊ ፈለጎችን በቁርኣን ንባቡ ውስጥ መተግበር ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡

ሀ. ረጋ ብሎ ማንበብ አለበት፡፡ ይህ ማለት መቸኮል የለበትም፡፡

ለ. ንባቡን  አንቀጽ በአንቀጽ መለያየት አለበት፡፡ ይህ ማለት ሁሉንም ሳያቋርጥ ሁለት፣ ሶስት አንቀጾችን አንድ ላይ እያያዘ ማንበብ የለበትም፡፡ ስለዚህ በእያንዳንዱ አንቀጽ መቆም አለበት፡፡

ሐ. አላህን በሚያጠራ  አንቀጽ ላይ ሲደርስ አላህን ከሚባሉና ከሚነገሩ ነገሮች ማጥራት፣ አላህን በሚጠይቁ አንቀጽ ላይ ሲደርስ አላህን መጠየቅ እንዲሁም በአላህ መጠበቅን በሚጠይቁ አንቀጾች ላይ ሲደርስ በአላህ መጠበቅን መጠየቅ አለበት፡፡

ከዚህ በላይ ላሳለፍነው ሃሳብ ማስረጃው፡- 

ሑዘይፋህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት፣ ‹‹ከእለታት አንድ ቀን ከነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ጋር አንዲት ሌሊት ሰገድኩ፡፡ ሰላታቸውን በአል-በቀራህ ምዕራፍ ጀመሩ፡፡ መቶኛው አንቀጽ ላይ ረኩዕ ያደርጋሉ አልኩ፡፡ -ንባባቸውን- ቀጠሉ፡፡ በዚያው ሌላ ረከዐህ ይሰግዳሉ አልኩ፡፡ አሁንም ቀጠሉ፡፡ አሁንም ሩኩዕ ያደርጋሉ አልኩ፡፡ የአን-ኢሳእን ምዕራፍ ጀመሩ፡፡ ከዚያ የኣል-ዒምራንን ምዕራፍ ጀመሩና አነበቡ፡፡ ረጋ ብለው ያነቡ ነበር፡፡ አላህን ከሚባሉ ነገሮች በሚያጠራ ቦታ ላይ ሲያልፉ አላህን ከሚባሉት ነገሮች ያጠራሉ፡፡ አላህን በሚጠይቅ አንቀጽ ላይ ሲያልፉ አላህን ይጠይቃሉ፡፡ ከአላህ ጥበቃን በመጠየቅ አንቀጽ ላይ ሲያልፉ በአላህ ይጠበቃሉ፡፡ ከዚያ ሩኩዕ አደረጉና፣ “በእጅጉ የላቀው ጌታዬ ጥራት ተገባው፡፡” አሉ፡፡ ረኩዐቸው ልክ እንደመቆማቸው ዓይነት ነበር፡፡ ከዚያም “አላህ ለሚያሰመሰግነው ምስጋናውን ሰማ፡፡” አሉና ከሩኩዐቸው ተነሱ፡፡  ከዚያም ልክ ከሩኩዐቸው ጋር የቀረበ መቆምን ቆሙ፡፡ ከዚያ ሱጁድ አደረጉና “እጅግ ልእልና የተገባው ጌታዬ ጥራት ተገባው” አሉ፡፡ ሱጁዳቸው ከመቆማቸው ጋር የተቀራረበ ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡  ሙሰሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (772) ላይ ዘግበውታል፡፡

አሕመድ -አላህ ይዘንላቸው- ሙስነድ በተሰኘው የሐዲሥ ዘገባቸው ከኡምሙ ሰለመህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት ስለየአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- የቁርኣን አነባብ (አቀራር) ተጠየቁ፡፡ እሳቸውም ‹‹ንባባቸው አንቀጽ አንቀጽ ይለያይ ነበር፡፡ {በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩኀ አዛኝ በኾነውõ ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት ጌታ ለኾነውõ እጅግ በጣም ሩኅሩኅ በጣም አዛኝõ የፍርዱ ቀን ባለቤት ለኾነውõ አንተን ብቻ እንግገዛለን፤ አንተንም ብቻ ርዳታን እንለምናለንõ ቀጥተኛውን መንገድ ምራንõ የነዚያን በነርሱ ላይ በጎ የዋልክላቸውን÷ በነሱ ላይ ያልተቆጣህባቸውንና ያልተሳሳቱትንም ሰዎች መንገድ (ምራን፤ በሉ)፡፡} አሕመድ አሕመድ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (26538) የዘገቡት ሲሆን  አድ-ዳረልቁጥኒይ በሐዲሥ ዘገባቸው “የዘገባ ሰንሰለቱ ትክክል ነው፡፡ አስተላለፊዎቹ ሁሉም እምነት የሚጣልባቸው ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡ አን-ነወዊም ትክክለኛነቱን አረጋግጠዋል፡፡  (አል-መጅሙዕ ገጽ ፡ 3 ገጽ ፡ 333)፡፡

brightness_1 ግለሰቡ አንዳንድ ጊዜ በዊትር ሰላቱ ላይ ቁኑት ማድረግ

"ቁኑት" ማለት ዱዓእ ማለት ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርገው የአል-ኢኽላስን ምዕራፍን በሚያነብበት ሶስተኛው ረከዐህ ላይ ነው፡፡ 

ቁኑትን የዊትር ሰላት ላይ አንዳንድ ጊዜ ማድረጉ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መተዉ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ ሸይኹ-ል-ኢስላም ኢብን ተይሚይየህ -የአላህ ይዘንላቸው- የመረጡትና ቅድሚያ የሚሰጠው ከማድረጉ አብዛኛውን ጊዜ መተዉ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ዊትር የሚሰግድ ሰው ቁኑት ላይ እጆቹን ከፍ ያደርጋልን?

ትክክለኛው አዎን በርግጥ እጆችን ከፈፍ ያደርጋል የሚለው ነው፡፡ ይህንንም አብዛኞቹ ዑለሞች ደግፈውታል፡፡ ይህም ከኢብን ዑመር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- የተረጋገጠ በመሆኑና በአል-በይሀቂይ የሐዲሥ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረ በመሆኑ ነው፡፡

አል-በይሀቂይ -አላህ ይዘንላቸው- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰሓቦች -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በቁኑት ላይ እጆቻቸውን ከፍ አድርገዋል፡፡›› (አስ-ሱነኑ-ል-ኩብራ ቅጽ፡ 2 ገጽ፡ 211ን ይመልከቱ)

ጥያቄ፡- ዊትር ላይ የሚያደርገውን ቁኑቱን በምን ይጀምራል?

ተመራጩ የዑለሞች አስተያየት -አላህ ይበልጥ ዐዋቂ ነው- አላህን በማመስገንና በማወደስ፣ ከዚያም በነቢዩ ላይ የአላህን እዝነተና ሰላምታ በማቅረብ መጀመሩ ነው፡፡ ከዚያ ዱዓእ ያደርጋል፡፡ ይህ ለጥያቄው በጣም የቀረበ መልስ ነው፡፡

ለዚህ ማስረጃው፡-

ፉዳለህ ኢብን ዑበይድ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይቀበላቸው- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹በነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ላይ የአላህን እዘነትና ሰላምታ ሳያወርድ ዱዓእ ሲያደርግ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሰሙትና፣ “ይህ ሰው ተቻኮለ፡፡›› አሉና ሰውዬውን ጠርተዉ ለእሱና ለሌሎችም እንዲህ አሉ፣ “አንዳችሁ ዱዓእ ካደረገ አላህን በማመስገንና በማወደስ ይጀምር፡፡ ከዚያ ነቢዩ ላይ የአላህን እዝነትና ሰላምታ ያወርድ፡፡ ከዚያ በኋላ ያሻውን ዱዓእ ያድርግ  አት-ቲርሚዚይ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (3477) ላይ ሐዲሡን የዘገቡ ሲሆን፤ ‹‹ይህ በመልካም ደረጃ ላይ የሚገኝ ትክክለኛ ሐዲሥ ነውም›› ብለዋል፡፡ 

ኢብን አል-ቀይዪም -አላህ ይዘንላቸው- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹በዱዓእ ላይ የሚወደደው ዱዓእ አድራጊው አላህን በማመስገን መጀመሩ፣ በጉዳዮች መካከል አላህን ማወደሱ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በፉዳለህ ኢብን ዑበይድ ሐዲሥ ላይ እንደተወሳው ጉዳዩን ይጠይቅ፡፡›› (አል-ዋቢሉ-ስሰይዪብ ገጽ፡ 110)

ጥያቄ፡- ከቁኑት ዱዓእ በኋላ ፊቱን በመዳፎቹ ያብሳልን?

ትክክለኛው፡- ትክክለኛ የሆነ ሐዲሥ ባለመኖሩ ምክንያት ከዱዓእ መጠናቀቅ በኋላ ፊትን ማበስ ነቢያዊ ፈለግ አይደለም የሚለው ነው፡፡

ኢማም ማሊክ -አላህ ይዘንላቸው- በዱዓእ ወቅት ፈቱን በመዳፎቹ ፊቱን ስለሚያብስ ሰው ሁኔታ ተጠየቁ፡፡ እሳቸውም ይህን አስተባበሉና፣ ‹‹አላወቅኩም›› አሉ፡፡ አል-ሚርወዚይ "አል-ዊትር"  ገጽ፡ 236፡፡

ሸይኹ-ል-ኢስላም -አላህ ይዘንላቸው- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹ፈቱን በመዳፎቹ ማበስን አስመልከቶ ማስረጃ የሚሆን አንድ ወይም ሁለት ሐዲሦች ፈጸሞ አልተዘገቡም፡፡›› አል-ፈታዋ ቅጽ፡ 22 ገጽ፡ 519፡፡

brightness_1 ቤተሰቡን ለሌሊት ሰላት መቀስቀስ

አንድ ሰው ቤተሰቡንና ሚሰቱን ለሌሊት ሰላት መቀስቀሱ እንዲሁም አንዲት ሴት ለሌሊት ሰላት ባሏንና  መቀስቀሷ ከነቢያዊ ፈለግ መካከል ነው፡፡ ይህ በመልካም ነገር ላይ የመተበባር አንዱ ምዕራፍ ነው፡፡

ለዚህ ማስረጃው፡-

ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እኔ በእሳቸውና በቂብላህ መካከል ተኝቼ የሌሊት ሰላታቸውን ይሰግዱ ነበር፡፡ ዊትር ሊሰግዱ ሲፈልጉ ይቀሰቅሱኛል እኔም ተነስቼ ዊትር እሰግዳለሁ፡፡›› ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (512)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (512) ዘግበውታል፡፡

ኡምሙ ሰለመህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁን- ከእንቅልፋቸው ነቁና፤ “ከሚባለው ከንቱና ውዳቂ የሆነ ነገር አላህ ጠራ ከሃብቱ ምንድን ወረደ፣ ከፈተናዎች ምንስ ወረደ፣ -ሚስቶቻቸውን ለመጥቀስ ፈልገውም- እስኪሰግዱ ድረስ የቤቶቹን ባለቤቶች ማነው ከእንቅልፋቸው የሚያነቃቸው ምናልባት በምድር ላይ የለበሰች የሆነች በወዲያኛው ዓለም እርቃን ትሆናለች፡፡”  አሉ፡፡›› ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (618) ዘግበውታል፡፡

 

brightness_1 ለሌሊት ሰላት የሚነሳ ሰው ለነፍሱ የሚራራ ሰው መሆን አለበት፡፡

- ድካም ከተሰማው ተቀምጦ ይሰግዳል፡፡

አነስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ወደመስጂድ ገቡ፡፡ በምሰሶዎች መካከል ገመድ ተዘርግቶ ነበር፡፡ “ይህ ምንድን ነው?” አሉ፡፡ ሰሓቦችም፤ ‹ለምትሰግደዋ ዘይነብ ነው፡፡ከተሳነፈች ወይም ከደከመች ትይዘዋለች፡፡› አሏቸው፡፡ እሳቸውም፤ “ፍቱት፡፡ አንዳችሁ በንቃት ውስጥ በሚሆንበት ወቅት ይስገድ፡፡ ከተሳነፈ ወይም ከተዳከመ ይቀመጥ፡፡" አሉ፡፡›› ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (784) ዘግበውታል፡፡

- እንቅልፍ ካንጎላጀው ንቁ ይሆን ዘንድ ይተኛ፡፡ ተኝቶ ሲነሳ የቻለውን ይስገድ፡፡

ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እንዲህ ብለዋል፤ “አንዳችሁ ሰላት ውስጥ ካንጎላጀ እንቅልፉ እስኪሄድለት ድረስ ይቀመጥ፡፡ አንዳችሁ እያንጎላጀ ከሰገደ ምናልባት አላህን ምህረት ለመጠየቅ ይሄድና ራሱን ሊስድብ ይችላል፡፡” ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (212)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (786)  ዘግበውታል፡፡

- ሌሊት ላይ ቁርኣን ሲቀራ ማንጎላጀት ወይም አንዳች ነገር ከተሰማው ብርታት ያገኝ ዘንድ መተኛቱ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡

አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- አንዲህ ብለዋል፤ “አንዳችሁ ሌሊት ላይ ተነስቶ ሲሰግድ ቁርአን አንደበቱ ላይ ባይተዋር ከሆነበትና ምን እንደሚል የማያውቅ ከሆነ ይተኛ፡፡”  ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (787) ዘግበውታል፡፡

brightness_1 በመጨረሻው የሌሊቱ አንድ ሶሰተኛ ክፍል ዱዓእ ማድረግ

በነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁን- ይዘወተሩ ከነበሩ የሌሊት ሰላት ነቢያዊ ፈለጎች መካከል ዱዓእ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ በመጨረሻው ላይ ዱዓእ ባያደርግም በሌሊቱ መጨረሻ ላይ ቁኑት ላይ የሚያደርገው ደዓእ ለአንድ ሰው በቂው ነው፡፡ በዚህ ወቅት ዱዓእ ማድረግ ከነቢያዊ ፈለጎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ወቅት ዱዓእ ምላሽ እንደሚያገኝ የተረጋገጠበት ወቅት ከመሆኑ ባሻገር ልእልና የተገባው የክብር ባለቤት አላህ ወደምድራዊ ሰማይ የሚወርድበት ወቅትም በመሆኑ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ቡኻሪና ሙስሊም ከአቢ ሁረይረህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በዘገቡት ሐዲሥ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹የተባረከውና ልእልና የተገባው ጌታችን የመጨረሻው ሌሊት አንድ ሶስተኛ ሲቀር ወደምድራዊው ሰማይ ይወርዳል፡፡ “ማነው የሚለምነኝ ምላሽ የምሰጠው፣ ማነው የሚጠይቀኝ የጠየቀኝን የምሰጠው፣ ማነው ምህረትን የሚጠይቀኝ ምህረትን የምለግሰው፡፡” ይላል፡፡›› ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1145) ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (758) ላይ ዘግበውታል፡፡

brightness_1 የዊተር ሰላቱን በሰላምታ ካጠናቀቀ በኋላ፣ ሶስት ጊዜ ‹‹ሱብሓነ መሊከ-ል-ቁዱስ›› /የተቀደሰው ንጉሥ በእሱ ላይ ከሚባለው ከንቱና ውድቅ የሆነ ነገር ሁሉ ጠራ፡፡/ ይልና ሶስተኛው ላይ ድምጹን ከፍ ያደርጋል፡፡

ዚህ ማስረጃው-

ኡበይ ኢብን ከዕብ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹የአላህ መልእከተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ዊትር ሰላት ላይ፣ {ሰብቢሒ-ስመ ረብቢከ-ል-አዕላ}ን፣ {ቁል ያ አይዩሀ-ል-ካፊሩዉን}ንና {ቁል ሁወ-ልላሁ አሐድ}ን ይቀሩ ነበር፡፡ ሰላታቸውን በሰላምታ ካጠናቀቁ በኋላ ሶሰት ጊዜ፣ “ሱብሓነ መሊከ-ል-ቁዱስ”  ይሉ ነበር፡፡›› አን-ነሳኢይ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1702) ሐዲሡን ሲዘግቡ ከዚህ በላይ እንዳሳለፍነው አል-አልባኒይ የሐዲሡን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡ ከዐብዱራሕማን ኢብን አብዛ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በተላለፈው ሐዲሥ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ‹‹ሱብሓነ መሊከ-ል-ቁዱስ›› ሲሉ በሶስተኛው ላይ ድምጻቸውን ከፍ ያደርጉ ነበር፡፡ አሕመድ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (15354)፣ አን-ነሳኢይ ደግሞ በቁጥር (1734) ሐዲሡን ሲዘግቡ  አል-አልባኒይ የሐዲሡን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡ ተሕቂቁ ሚሽካቱ-ል-መሳቢሕ ቅጽ፡ 1 ገጽ ፡ 389፡፡