brightness_1
ወደመጸዳጃ ቤት ሲገቡና ሲወጡ በሐዲሥ የተዘገቡ ዚክሮችን ማለት፡፡
ወደመጸዳጃ ቤት የሚገባ ሰው በትክክለኛ የሒዲሥ ዘገባዎች የሠፈሩት ቃላት ማለቱ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡
ከአነስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተወራው፣ ‹‹የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ወደመጸዳጃ ቤት ሲገቡ፣ “አልላሁምመ ኢንኒ አዑዙ ቢከ ሚነልኹቡሢ ወልኸባኢሢ፡፡ /አላህ ሆይ! እርኩስ ከሆኑ ወንድ፣ እርኩስ ከሆኑ እንስት ሸይጣኖች ባንተ እጠበቃለሁ፡፡/” ይሉ ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (6322)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (375) ላይ ዘግበውታል፡፡
‹‹ኹቡሥ›› ማለት ወንድ ሸይጣኖች ማለት ሲሆን ‹‹ኸባኢሥ›› ደግሞ እንስት (ሴት) ሸይጣኖች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጥበቃ የሚያስፈልገው ከወንድ ሸይጣኖችና ከሴት (እንስት) ሸይጣኖችም ነው፡፡
ቃሉ ‹‹ኹብሥ›› ተብሎ ከተነበበ ትርጉሙ እርኩስና መጥፎ ከሆኑ መናፍስት እንዲሁም ከተንኮልና ከተንኮለኞች ጥበቃን መጠየቅ ማለት ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ ማለቱ ሁሉንም የሚያጠቃል በመሆኑ ተመራጭ ነው፡፡
- ከመጸዳጃ ቤት የሚወጣ ሰው ሲወጣ የሚከተለውን ማለቱ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡-
ሙስነድ በተሰኘው የአሕመድ የሐዲሥ መድብል ላይ እንዲሁም በአቢ ዳዉድና አት-ቲርሚዚይ የሐዲሥ ዘገባ ላይ እንደሰፈረውና አል-አልባኒይ ትክክለኛቱን ባረጋገጡት የዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ሐዲሥ ዓኢሻ፣ ‹‹የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ከመጸዳጃ ቤት ሲወጡ፣ “ጉፍራነክ፡፡ /ጌታዬ ሆይ! ምሕረትህን ለግሰኝ፡፡/” ይሉ ነበር፡፡ አሕመድ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (25220)፣ አቡ ዳዉድ በቁጥር (30) እንዲሁም አት-ቲርሚዚ በቁጥር (7) የዘገቡት ሲሆን አል-አልባኒይ የሐዲሡን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡ ተሕቂይቁ ሚሽካቱ-ል-መሳቢይሕ ቅጽ ፡ 1 ገጽ፡ 116፡፡