ጫማ ሲጫሙ በቀኝ መጀመር ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡
አንድ ሙስሊም ጫማዎቹን ለመጫማት ሲፈልግ በቀኝ መጫማት መጀመሩ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ በተቃራኒው ሲያወልቅ በግራው ማውለቅ መጀመሩ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡
ለዚህም ማስረጃው፡- አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንዳችሁ ከተጫማ በቀኙ ይጀምር፡፡ ሲያወልቅ ደግሞ ግራው ያውልቅ፡፡ ቀኝ እጁ በመጫማት ላይ ቀዳሚ ይሁን፡፡ በማውለቅ ላይ ደግሞ መጨረሻ ይሁን፡፡” ብለዋል፡፡ ቡኻሪ በቁጥር (5856) ላይ ዘግበውታል፡፡
በእነዚህ ሁለት ሐዲሦች ውስጥ ሶስት ነቢያዊ ፈለጎችን እናገኛለን፡፡ እነርሱም፡-
1- ሰጫሙ በቀኝ መጀመር
2- ሲያወልቁ በግራ መጀመር
3. የሁለቱንም እግር ጫማ መልበስ ወይም አንድ ጫማ ብቻ ተጫምተው እንዳይሄዱ ሁለቱንም ጫማዎች ማውለቅ፡፡ ይህም በሌላ ዘገባ ላይ፣ “አንዳችሁ በአንድ ጫማ አይሂድ፡፡” በሚል ሐዲሥ መከልከሉ ተዘግቧል፡፡
ነጫጭ የሆኑ ልብሶችን መልበስ ነቢያዊ ፈለግ ነው
የዚህ ርዕስ መልእክት አንድ ሰው ካሉት በተለያዩ ቀለማት የተቀለሙ ልብሶች መካከል (ነጭ) ልብስ መልበሱ ከነቢያዊ ፈለጎች መካከል አንዱ ነው የሚል ነው፡፡ ኢብን ዐብባስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ከልብሶቻችሁ ነጩን ልብስ ልበሱ፡፡ በእርግጥ መልካሙ ልብሳችሁ ነው፡፡ በእርሱም ሙታኖቻችሁን ከፍኑ፡፡” ብለዋል፡፡ አሕመድ በቁጥር (2219)፣ አቡ ዳዉድ በቁጥር (3878)፣ አት-ቲርሚዚይ በቁጥር (994) የዘገቡት ሲሆን አል-አልባኒይ ትክክለኛነቱን ዘግበውታል፡፡ ሰሒሑ-ልጃሚዕ ቅጽ ፡ 1 ገጽ ፡ 267፡፡
ሸይኻችን ኢብን ዑሠይሚን -አላህ ይዘንላቸው- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹ይህ ሐዲሥ እንደቀሚሶች፣ ሸርጦች፣ ሱሪዎች ያሉትን ነጭ ልብሶችን ያጠቃለለ ነው፡፡ ሁሉም ግን ነጭ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ በጣም ተመራጭ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ሰው ካሉት ልብሶች መካከል ሌላ ቀለም ያላቸውን ልብሶች ቢለብስ ምንም ችግር የለውም፡፡ የሚለብሳቸው ልብሶች ግን ለሴቶች ተብለው የተለዩ አለመሆናቸው በመስፈርተነት የተቀመጠ ነው፡፡›› ሸርሑ ረያዱ-ስሳሊሒን ቅጽ ፡ 2 ገጽ ፡ 1087፡፡
ሽቶ መቀባት ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡
አነስ -አላህ መልካም ሠራዎቻቸውን ይውደዳቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ከምድራዊው ዓለም በእኔ ዘንድ ሰቶች፣ ሽቶ እጅግ የተወደዱ ተደርገውልኛል፡፡ የዓይን ማረፊያዬ በሰላት ውስጥ እንዲሁ ተደርጎልኛ፡፡” ብለዋል፡፡ አሕመድ በቁጥር (12293)፣ አን-ነሳኢይ በቁጥር (3940) የዘገቡት ሲሆን አል-አልባኒይ በሰሒሑ አን-ነሳኢይ ውስጥ ሐዲሡን ‹‹ሐሰኑን ሰሒሕ›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን፣ “ከምድራዊው ዓለማችሁ በእኔ ዘንድ ሶስት ነገሮች የተወደዱ ተደርገውልኛል፡፡” የሚለው ዘገባ የሐዲሡ ደረጃ ደካማ ነው፡፡
ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ከእሳቸው ላይ መጥፎ ጠረን መኖርን ይጠሉ ነበር፡፡ ቡኻሪ ከዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በዘገቡት ረዥም ሐዲሥ ውስጥ ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ከእሳቸው ላይ ሽታን ማግኘት ይበረታባቸው ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሽታን ማግኘት ይበረታባቸው ነበር፡፡›› ማለት ጥሩ ያልሆነ ሽታን ማግኘት ማለት ነው፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (6972) ላይ ዘግበውታል፡፡
ሽቶን መመለስ ይጠላል
አነስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሽቶን አይመልሱም ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2582) ላይ ዘግበውታል፡፡
ጸጉርን በሚያበጥሩበት ወቅት በቀኝ መጀመር ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡
ጸጉርን በሚያበጥሩበት ወቅት በቀኝ ጎን መጀመርና ከዚያም በግራ መቀጠል ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡
ለዚህ ማስረጃው፡-
ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ጸጉራቸውን በሚያበጥሩበት፣ ዉዱእ በሚደርጉበትና በሁሉም ነገሮቻቸው በቀኝ መጀመር ያስድሰታቸው ነበር፡፡›› ብለዋል፡፤ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (168)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (268) ላይ ዘግበውታል፡፡