አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንድ ሰው የጀማዐህ ሶላት ቤቱ ወይም መገበያያው ውስጥ ከሚሰግደው ሶላት በሃያ አምስት እጥፍ ይበልጣል፡፡ ይህም ውዱእ ካደረገ ውዱኡንም ካሳመረ ከዚያም ወደ መስጂድ ለሶላት ሲል ብቻ ከወጣ፣ አንድ እርምጃ አይራመድም በእሷ (በእርምጃዋ) ምክንያት አንድ ደረጃ ከፍ ያለለት አንዲት ሃጢአት የተሰረዘለት ቢሆን እንጂ፡፡ በሚሰግድ ጊዜ የሰገደበትን ቦታ እስኪለቅ ድረስ ውዱእ ሳያፈርስ (ሳያበላሽ) በመስገጃው ላይ ከሆነ መላኢኮች “አላህ ሆይ! ረድኤትህን በእሱ ላይ አውርድ፣ እዘንለትም፡፡” በማለት ዱዓ ያደርጉለታል፡፡ (ከሰገደው ሶላት ሌላ) ሶላት እስከተጠባበቀ ድረስ ሶላት ውስጥ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡”ብለዋል፡፡ ሙሰሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (649) ላይ ዘግበውታል፡፡
አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደስተላለፉት ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ወደሰላት የመግባት ጥሪን በሰማችሁ ጊዜ ወደሰላት ሂዱ፡፡ በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ መሄድን አደራችሁን፡፡ ሰላትንም እስካገኛችሁ ድረስ አትቸኩሉ፡፡ ያለፋችሁን አሟሉ፡፡” ብለዋል፡፡ ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (636)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (602) ላይ ዘግበውታል፡፡
አን-ነወዊይ -አላህ ይዘንላቸው-፣ ‹‹የሰከነ መንፈስ ማለት እርምጃዎችን በቀስታ ማምጣትና ጨዋታን መራቅ ማለት ሲሆን እርጋታ ማለት እይታን እንደመሰብሰብ፣ ድምጽን መቀነስና ከወዲያ ወዲህ እንዳለመዞር ዓይነት ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ አን-ነወዊይ፡- ሸርሑ ሙስሊም ሐዲሥ ቁጥር (602) ‹‹ወደሰላት በርጋትና በሰከነ መንፈስ መምጣት የመወደዱና እየሮጡ መምጣት የመጠላቱ ምዕራፍ››
አነስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹መስጂድ ውስጥ ስትገባ በቀኝ እግርህ መጀመር፣ ስትወጣ ደግሞ በግራ እግርህ መጀመርህ ከነቢያዊ ፈለጎች መካከል ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ አል-ሐኪም በሐዲሥ ዘገባ መድብላቸው ቅጽ፡ 1 ገጽ፡ 338 ላይ ሲዘግቡ በሙስሊም የዘገባ መሰፈርትነት የሐዲሡንም ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡ይህም ከኢብን ዑመር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በተላለፈው ሐዲሥ መሠረት ቡኻሪ [መስጂድም ሆነ ሌላ ሥፍራ ሲገባ በቀኝ መጀመር በሚለው ምዕራፍ ሥር ኢብን ዑመር መስጂድ ሲገቡ በቀኝ እንደሚጀምሩ፣ ሲወጡ ደግሞ በግራ እንደሚጀምሩ] አስፍረዋል፡፡ ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹የአላህ መልእከተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- በሁሉም ሁኔታዎቻቸው ላይ በቀኝ መጀመርን ይወዱ ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (168)፣ ሙሰሊም ደግሞ በቁጥር (268) ላይ ዘግበውታል፡፡
ይህ ለሰላቱ በጊዜ ከመጣ ነው፡፡ ከመጣም ሁለት ረከዐዎችን ሳይሰገድ መቀመጥ የለበትም፡፡ አቢ ቀታዳህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንዳችሁ መስጂድ ውስጥ ከገባ ሁለት ረከዐዎችን ሳይሰግድ አይቀመጥ፡፡” ብለዋል፡፡ ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (1163)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (714) ላይ ዘግበውታል፡፡
እንደየአል-ፈጅር፣ አዝ-ዙህር ሰላቶች ከሰላቱ በፊት የሚሰገድ የሱንና ሰላት ካለ ፣ ወይም መስጂድ ውስጥ በጠዋት የአድ-ዱሐ ሰላት ለመስገድ የገባ ወይም ዊትርን ወይም ግዴታ የሆነን ሰላት መስጂድ ውስጥ ከሰገደ ለተሒየቱ-ል-መስጂድ በቂው ነው፡፡ ምክንያቱም የተሒየቱ-ል-መስጂድ ዓላማ፡- አንድ ሰው መስጂድ ከገባ በኋላ ሁለት ረከዐህ ሳይሰገድ እንዳይቀመጥና መሰጂድን በሰላት ማሳዋብና ከሰላት ውጭ መስጂድ እንዳይተው ነው፡፡
ለወንዶች በመጀመሪያው ሰልፍ ላይ መቻኮላቸው ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሰልፍ በላጩ የሰላት ሰልፍ ነው፡፡ ለሴቶች በላጩ ሰልፍ ደግሞ የሰላቱ የመጨረሻ ሰልፍ ነው፡፡
አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ከወንዶች ረድፎች መካከል በላጩ ረድፍ የመጀመሪያው ነው፡፡ መጥፎው ደግሞ የመጨረሻው ነው፡፡ ከሴቶች ረድፎች መካከል በላጩ ረድፍ የመጨረሻው ነው፡፡ መጥፎው ደግሞ የመጀመሪያው ነው፡፡” ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (440) ዘግበውታል፡፡ በላጩ፡- ማለት በርካታ ምንዳና ትሩፋትን የሚያስገኝ ማለት ሲሆን መጥፎዋ፡- ማለት ደግሞ ዝቅተኛ ምንዳና ትሩፋት የሚያስገኝ ማለት ነው፡፡
ይህ ሐዲሥ ወንዶችና ሴቶች ግርዶሽ በሌለበት ሁኔታ ሰላትን በሕብረት (ጀማዐህ) የሚሰግዱ ከሆነ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ለሴቶች የሰላቱ የመጨረሻ ረድፍ በላጭ ነው፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን ከወንድ ዓይኖች እንዲጠበቁ ምክንያት ይሆንላቸዋልና ነው፡፡ እንደግርግዳና ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉት ዓይነት ግርዶሽ ያለበት ሥፍራ ወይም ልክ ለሴች መስገጃ ይሆን ዘንድ ልዩ ክፍል እንደሚዘጋጅባቸው አብዛኛዎቹ መስጂዶቻችን ዓይነት ከሆነ ለሴቶች በላጩ ረድፍ የመጀመሪያው ነው፡፡ ይህም ከወንዶች እኩል ይሆኑ ዘንድ ለማስቻል ነው፡፡ በማንኛውም የመጀመሪያ የሰላት ረድፍን አስመልከቶ የተዘገቡ ሐዲሦች በርካታ ናቸው፡፡ ከእነርሱም መካከል፡-
አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ሰዎች በአዛንና በመጀመሪያ ረድፍ ውስጥ ያለውን ምንዳ ቢያውቁ ኖሮና እሱ ላይ እጣ ከመጣጣል በስተቀር ሌላ የማያገኙ ቢሆን እጣ ይጣጣሉ ነበር፡፡ ሰዎች በመክፈቻው ተክቢራ ውስጥ ያለውን ቢያውቁ ኖሮ ወደርሱ ይሽቀዳደሙ ነበር፡፡ በምሽት -በዒሻእ- እና በሱብሒ ሰላቶች ውስጥ ያለውን ቢያውቁ ኖሮ እየዳሁም ቢሆን ይመጡ ነበር፡፡” ብለዋል፡፡ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (615)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (437) ላይ ዘግበውታል፡፡
ከዚህ በላይ እንደሳለፍነው ኢማሙን ተከትሎ ለሚሰግድ ሰው ለሰላቱ ተመራጩ ረድፍ የመጀመሪያው ረድፍ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ተከታዩ ለኢማሙ ቀረብ ለማለት መጣር ይኖርበታል፡፡ ለኢማሙ በቀኝ በኩልም ሆነ በግራ በኩል መሆን በላጭ ነው፡፡
ለዚህ ማስረጃው፡-
ዐብዱላህ ኢብን መስዑድ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ከናንተ መካከል የእውቀትና የአእምሮ ባሌቶች የሆኑ ይቅረቡኝ፡፡” ብለዋል፡፡ አቡ ዳዉድ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (674)፣ አት-ቲርሚዚይ ደግሞ በቁጥር (228) ላይ ዘግበውታል፡፡ ይህ ሐዲሥ በማንኛውም አቅጣጫ በኩል ለኢማሙ ቅርብ መሆን ተፈላጊ ለመሆኑ ማሰረጃ ነው፡፡