አዛንን መከታተል
አዛንን የሚሰማ ሰው ሐይየ ዐለ-ስሰላህና ሐይየ ዐለ-ል-ፈላሕ ከሚለው በስተቀር ሙአዚኑ እንደሚለው ማለቱ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ ሐይየ ዐለ-ስሰላህና ሐይየ ዐለ-ል-ፈላሕ ላይ ግን ‹‹ላ ሐውለ ወላ ቁውወተ ኢልላ ቢልላህ›› ይላል፡፡
ዐብዱላህ ኢብን ዐምር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- “ሙአዚንን ከሰማችሁ እንደሚለው ዓይነት በሉ፡፡…” ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (384) ዘግበውታል፡፡ ከዑመር ኢብን አል-ኸጣብ (ረ.ዐ) እንደተወራው የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- “አንድ ሙአዚን ‹‹አላሁ አክበር አላሁ አክበር›› ሲል አንዳችሁ “ከልቡ አላሁ አክበር አላሁ አክበር” ካለ፣ (ሙአዚኑ) ‹‹አሽሀዱ አን ላኢላሀ ኢልለላህ›› ሲል (አንዳችሁ) ‹‹አሽሀዱ አን ላ ኢላሀ ኢልለላህ›› ካለ፣ (ሙአዚኑ) ‹‹አሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ረሱሉላህ›› ሲል (አንዳችሁ) ‹‹አሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ረሱሉላህ›› ካለ፣ (ሙአዚኑ) ‹‹ሐይየ ዐለ-ስሰላህ›› ሲል (አንዳችሁ) “ላ ሐውለ ወላ ቁውወተ ኢልላ ቢልላህ” ካለ፣ (ሙአዚኑ) ‹‹ሐይየ ዐለል-ፈላሕ›› ሲል (አንዳችሁ) ‹‹ላ ሐውላ ወላ ቁውወተ ኢልላ ቢልላህ›› ካለ፣ (ሙአዚኑ) ‹‹አላሁ አክበር አላሁ አክበር›› ሲል (አንዳችሁ) ‹‹አላሁ አክበር አላሁ አክበር›› ካለ፣ (ሙአዚኑ) ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለላህ ሲል (አንዳችሁ) ላ ኢላሀ ኢልለላህ›› ካለ ጀነት ገብቷል፡፡” ብለዋል፡፡ ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (385) ዘግበውታል፡፡
ለፈጅር ሰላት በማነሳሺያ ቃላት ወቅት አዛኑን የሚከታተል ሰው ሙአዚኑ እንደሚለው ‹‹አስ-ሰላቱ ኸይሩን ሚነ-ንነውም›› ይላል፡፡
የሚከተለውን ዚክር ከሸሃደተይን በኋላ ማለት፡-
ሙአዚኑ ሁለተኛው ላይ ‹‹አሽሀዱ አን-ላ ኢላሀ ኢልለላህ›› ካለ በኋላ ከሰዕድ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- የተላለፈውና የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እንዲህ ያሉትን ዚክር ማለት ነቢያ ፈለግ ነው፡፡ “አንድ ሙአዚን አዛን ሲያደርግ የሰማ ሰው ከዚያም “አሽሀዱ አን ላ ኢለሀ ኢልለላህ ወሕደሁ ላ ሸሪከ ለሁ ወአንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ ረዲይቱ ቢልላሂ ረብበን ወቢ ሙሐመደን ረሱለን ወቢል ኢስላሚ ዲይነን” ያለ ሃጢአቱ ተምሮለታል፡፡” ብለዋል፡፡ ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (386) ዘግበውታል፡፡
ከአዛን በኋላ በነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ላይ ሰላዋት ማድረግ፡፡
ከዐብደላህ ኢብን ዐምር ኢብን አልዓስ (ረ.ዐ) እንደተወራው የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)፣ “አንድ አዛን የሚያደርግ ሰው (ሙአዚን) አዛን ሲያደርግ ከሰማችሁ (እሱ) እንደሚለው በሉ፡፡ ከዚያ በእኔ ላይ ሰለዋት አድርጉ፡፡ በርግጥ በእኔ ላይ አንድ ሰለዋት ያደረገ አላህ በእርሱ ላይ አስር ሰለዋት ያደርግለታል፡፡ ከዚያ የላቀውን ደረጃ (ከአላህ) ጠይቁልኝ፡፡ ይህች ደረጃ ከአላህ ባሪያዎች መካከል ለአንዱ ካልሆነች በስተቀር ለማንም የተገባች አይደለችም፡፡ ስለዚህ ይህ የአላህ ባሪያ እኔ እሆን ዘንድ እሻለሁ፡፡ ይህችን የላቀች ደረጃ ለእኔ የጠየቀልኝ ሰው በእርሱ ላይ አማላጅነቷ ተረጋገጠችለት፡፡” ሲሉ በርግጥ መሰማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (384) ዘግበውታል፡፡
በላጭ የሆነው ሰለዋት፡- ሰላቱ አል-አብራሂሚይየህ ነው፡፡ ይኸውም፡- ‹‹አላህ ሆይ! በሙሐመድ ላይና በሙሐመድ ቤተሰቦች ላይ እዝነት አድርግ፡፡ በኢብራሂም ላይና በኢብራሂም ቤተሰቦች ላይ እዝነት እንዳደረግከው ሁሉ…››
ከአዛን በኋላ የሚባሉ ዱዓዎችን ማለት
ከጃቢር ኢብን ዐብዱላህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተወራው የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “ጥሪውን በሚሰማ ጊዜ፤ ‹‹አልላሁምመ ረብበ ሀዚሂ-ድዳዕወቲ አት-ታምመህ ወስ-ሰላቲ-ል-ቃኢመህ ኣቲ ሙሐመደኒ-ል-ወሲለተ ወል ፈዲይለህ ወብዐሥሁ-ልላሁምመ መቃመ መሕሙውደኒ-ልለዚይ ወዐድተህ›› /የዚህች ምሉዕ የሆነች ጥሪና የምትሰገደው ስላት ጌታ የሆንከው አላህ ሆይ! ለሙሐመድ ከፍ ያለ ደረጃንና ልቅናን ስጣቸው፡፡ የተመሰገነችውን የላቀች ስፍራም ቃል በገባህላቸው መሠረትም ቀስቅሳቸው፡፡ ያለ በትንሳኤ እለት አማላጅነቴ ተረጋገጠችለት፡፡” ብለዋል፡፡ ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (614) ዘግበውታል፡፡
ከአዛን በኋላ ዱዓእ ማድረግ፡-
ዐብዱላህ ኢብን ዐምር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹አንድ ሰው ፣ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ሙአዚኖች ይበልጡናል፡፡›› አላቸው፡፡ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- “እንደሚሉት በል፡፡ ከጨረስክ በኋላም ጠይቅ ይሰጥሃል፡፡” አሉ፡፡ አቡ ዳዉድ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (524) ሐዲሡን ሲዘግቡት ኢብን ሐጀር የዘገባው ደረጃ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡ (ነታኢጁ-ል-አፍካር ቅጽ ፡ 1 ገጽ፡ 367) አል-አልባኒይም ትክክለኛነቱን አረጋግጠዋል፡፡ (ሰሒይሑ-ል-ከሊሙ-ጥጠይብ ገጽ ፡ 73)
አነስ ኢብን ማሊክ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “በአዛንና በኢቃማህ መካከል የሚደረግ ዱዓ ተመላሽ አይሆንም፡፡” ብለዋል፡፡ አን-ነሳኢይና በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (9895) የዘገቡት ሲሆን ኢብን አል-ኹዘይመህ ትክክለኛነቱን አረጋግጠዋል፡፡ (ቅጽ ፡ 1 ገጽ ፡ 221 እና 425)