ዉዱእ ወይም ከመጉመጥመጥ በፊት መፋቅ፡፡ ይህ ነቢያዊ ፈለግን የተከተለ ጥርስን የመፋቂያ ወቅት ነው፡፡ -ይህን ርዕስ ከዚህ በላይ አሳልፈንዋል-፡፡ ዉዱእ ማድረግ የፈለገ ሰው ጥርሱን መፋቅ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ ይህም ከአቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በተላለፈው ሐዲሥ ነቢ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ ‹‹በሕዝቦቼ ላይ ባላስቸግር ኖሮ ከሁሉም ዉዱእ ጋር መፋቂያን ባዘዝኳቸው ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ኢብን ኹዘይማህ በሐዲሥ ዘገባ መድብላቸው (ቅጽ፡ 1፣ ሐዲሥ ቁጥር፡ 73፣ ገጽ፡140)፣ አል-ሓኪም በሐዲሥ ዘገባ መድብላቸው ( ቅጽ፡ 1 ገጽ፡ 245) ላይ ዘግበውታል፡፡ ቡኻ ‹‹እርጥብና ደረቅ መፋቂያ›› በሚል ርእስ በሐዲሡ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ከዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተላለፈው እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹መፋቂያቸውንና ዉዱእ የሚያደርጉበትን ውሃ እናዘጋጅላቸው ነበር፡፡ አላህ ሊያነቃቸው የሻው ሌሊት ላይ ያነቃቸዋል፡፡ ጥርሳቸውን ይፍቃሉ፣ ዉዱእ ያደርጋሉ፣ ይሰግዳሉም፡፡…›› ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (746) ላይ ዘግበውታል፡፡
የነቢዩን -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- የዉዱእ አደራረግ አስመልከቶ ከዑሥማን ኢብን ዐፍፋን -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተላለፈው፣ ዑሥማን ዉዱእ የሚያደርጉበት ውሃ እንዲመጣላቸው አደረጉ፡፡ ዉዱእ አደረጉ፡፡ መዳፎቻቸውንም ሶሰት ሶስት ጊዜ አጠቡ…፡፡ ከዚያም፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ይህን ዉዱዬን በመሰለ ሁኔታ ዉዱእ ሲያደርጉ ተመልክቻለሁ፡፡›› አሉ፡፡ ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (164)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (226) ላይ ዘግበውታል፡፡
ከዑሥማን -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተላለፈው ‹የነቢዩን -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- የዉዱእ አደራረግ ሲገልጹ፣ ‹‹…ተጉመጠመጡ ከዚያ ውሃ ወደአፍንጫቸው ስበው አስወጡ ከዚያም ፊታቸውን ሶሰት ሶስት ጊዜያት አጠቡ፡፡…›› ብለዋል፡፡ ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (199) ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (226) ዘግበውታል፡፡ ወዱእ የሚያደርገው ሰው ፊቱን ከታጠበ በኋላ መጉመጥመጡንና ውሃ ወደአፍንጫው ስቦ ማስወጣቱን ቢያዘገይም ይፈቀዳል፡፡
ከለቂጥ ኢብን ሰቡረህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተላለፈው ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እንዲህ አሏቸው፣ ‹‹ዉዱእን አሟላ፤ በጣቶች መካከል ፈልፍል፣ ጾመኛ ካልሆንክ በስተቀር ውሃን ወደአፍንጫ በማስገባቱ ድንበር እለፍ፡፡›› አሕመድ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (17846)፣ አቡ ዳዉድ በቁጥር (142) ዘግበውታል፡፡ ኢብን ሐጀር፣ ‹‹ይህ ሐዲሥ ትክክል ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ አል-ኢሳበህ (ቅጽ፡ 9 ገጽ፡ 15)፡፡ በመጉመጥመጥ ላይ ድንበር ማለፍ የተወሰደው ‹‹ወዱእን አሟላ፡፡›› ከሚለው ቃል ነው፡፡
ግለሰቡ የራስ ቅሉን በሚያብስበት ወቅት እጆችን በራሱ ቅሉ ፊት ለፊት ላይ ያስቀምጣል፡፡ ከዚይም ከፊት ለፊት ጀምሮ ወደአናቱ ያብሳል፡፡ ከዚያው ወደተበሳበት ስፍራ ይመልሳቸዋል፡፡ ሴትም እንዲሁ ይህኑ ነቢያዊ ፈለግ በዚሁ ዓይነት ትፈጽማለች፡፡ ከአንገት በታች የወረደው የሴት ጸጉር አይታበስም፡፡
ይህን የሚያመለክተው ማስረጃ፡-
ዐብዱላህ ኢብን ዘይድ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው የነቢዩን -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ዉዱእ አደራረግ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹… ከራስ ቅላቸው መጀመሪያ ጀመሩ ከዚያ ወደአናታቸው ደርሰው ወደጀመሩበት እስኪመለሱ በእጆቻቸው አበሱ፡፡›› ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (185) ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (235) ላይ ዘግበውታል፡፡
የመጀመሪያው እጥበት ግዴታ ሲሆን ሁለተኛውና ሶስተኛው ደግሞ ነቢያዊ ፈለጎች ናቸው፡፡ ከሶሰት በላይ አይጨመርም፡፡
ይህን የሚያመለክተው ማስረጃ፡-
በቡኻሪ በተዘገበውና ከኢብን ዐብባስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተላለፈው፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- አንድ ጊዜ ወዱእ አደረጉ፡፡›› ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (157) ሲዘግቡ ከዐብዱላህ ኢብን ዘይድ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በዘገቡት ሐዲሥ ደግሞ፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሁለት ሁለት ጊዜ ወዱእ አደረጉ፡፡›› ብለዋል፡፡ ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (159) ዘግበውታል፡፡ ቡኻሪና ሙስሊም ከዑሥማን -አላህ መልካም ሥራዎቻቸው ይውደድላቸው- በዘገቡት ሐዲሥ፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሶስት ሶሰት ጊዜ ዉዱእ አድርገዋል፡፡›› ቡኻሪ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (159) ላይ ዘግበውታል፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ መቀያየሩ ይበልጥ ተመራጭ ነው፡፡ ይኸውም እንዳንድ ጊዜ አንድ ጊዜ፣ አንዳንድ ጊዜ ሁለት ሁለት ጊዜ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሶስት ሶሰት ጊዜ ይትቡ ነበር፡፡ ልክ በዐብዱላህ ኢብን ዘይድ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በተላለፈው ሐዲሥ መሰረት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለምሳሌ ፊታቸውን ሶስት ሶሰት ጊዜ ሲያጥቡ እጆቻቸውን ሁለት ጊዜ እንዲሁም እግሮቻቸውን አንድ ጊዜ ያጥቡ ነበር፡፡ ዛዱ-ል-ሚዓድ (ቅጽ፡ 1 ገጽ፡ 192)፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ሶስት ሶሰት ጊዜ በማሟላት ዉዱእ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ የነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- አስተምህሮ ነው፡፡
ከዑመር ኢብን አል-ኸጣብ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደተላለፈው የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹ከመካከላችሁ ማናችሁም ወዱእ አድርጎና ዉዱኡን አዳርሶ - ወይም አሟልቶ- ከዚያ ከአላህ በስተቀር አምላክ የለም፣ ሙሐመድም የእሱ ባሪያና መልእክተኛ ናቸው ብየዬ እመሰክራለሁ አይልም ለእሱ ሰምንቱ የጀነት በሮች የተከፈቱለትና ከእነሱም መካከል በፈለገው የገባ ቢሆን እንጂ፡፡›› ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (234) ዘግበውታል፡፡
ከአቢ ሰዒድ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይቀበላቸው- እንደተላለፈው የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹ወዱእ አድርጎና ወዱኡን ካጠናቀቀ በኋላ፣ “ጥራት የተገባህ አላህ ሆይ! በምስጋናህ ይሁን ካንተ በስተቀር አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ፡፡ ምህረትን እጠይቃለሁ ወዳንተም በንሰሐ እመለስልሃለሁ” ያለ ይህችን ቃሉን አላህ ማሕተም ይመታባታል፡፡ ከዚያም ከዐርሽ ሥር እስክትደርስ ድረስ ክፍ ትደረጋለች፡፡ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ አትሰበርም፡፡›› አን-ነሳኢይ ዐመሉ-ል-የውሚ ወልለይለህ (ገጽ ፡ 147፣ እንዲሁም አል-ሓኪም በሐዲሥ ዘገባ መድብላቸው (ቅጽ፡ 1 ገጽ፡ 752) ላይ ዘግበውታል፡፡ ኢብን ሐጀር -አላህ ይዘንላቸው- የዘገባውን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡ ነታኢጁ-ል-አፍካር ቅጽ፡ 1 ገጽ ፡ 246፡፡