ከዙህር በፊትና በኋላ የሚሰገዱ ሱንናዎች
ከዚህ በላይ በፍላጎት በሚፈጸሙ ነቢያዊ ፈለጎች ርዕስ ላይ ከዙህር በፊት አራት ረከዐህ፣ ከዙህር ሰላት በኋላ ሁለት ረከዐህ ሰላቶች መስገድ እንዳለ ተመልክተናል፡፡ ለዚህም የዓኢሻህ፣ የኡምሙ ሐቢባህ፣ የኢብን ዑመር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸው ይውደድላቸው- ሐዲሥ በማስረጃነት ተቀምጧል፡፡
የዙህር ሰላት ላይ የመጀመሪያውን ረከዐህ መቆም ከሁለተኛው ረከዐህ መቆም ማስረዘም ከነቢያዊ ፈለጎች መካከል ነው፡፡
አቢ ሰዒይድ አል-ኹድሪይ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹ለዙህር ሰላት ኢቃም ይደረጋል፡፡ የሚሄድ የፈለገ ወደበቂዕ ይሄዳል፡፡ ጉዳዩን ከፋጸመ በኋላ ዉዱእ ያደርጋል፡፡ ከዚያ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- የሚያረዝሙት የመጀመሪያው ረከዐህ ላይ ሳሉ ዘንድ ይመጣል፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (545) ላይ ዘግበውታል፡፡
ስለዚህ አንድ የዙህር ሰላትን የሚያሰግድ ሰው የመጀመሪያውን ረከዐህ ማርዘሙ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ ሰውዬው ለብቻው ቢሰግድም እንደሁ ነው፡፡ ማንኛዋም ሴት ብትሆን ለዙህር ሰላት ስትቆም ይህን ማድረግ አለባት፡፡ ይህ እየተረሳ የመጠ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ አላህ ነቢያዊ ፈለግን በተሟላ ሁኔታ የምንተገበርና የምንጠብቅ እንዲያደርገን እንለምነዋለን፡፡
በጣም ሞቃትማ በሚሆንበት ጊዜ ሙቀቱ ጋብ እስከሚል ድረስ ማዘግየት ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡
ለዚህ ማስረጃው፡-
አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝንትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ሙቀቱ ከበረታ ሰላትን አቀዝቅዙ፡፡ የሙቀት በርቱነት ከጀሃነም እስትንፋስ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (533፣534)፣ ሙሰሊም ደግሞ በቁጥር (615) ላይ ዘግበውታል፡፡
ሸይኽ ኢብን ዑሠይሚን -አላህ ይዘንላቸው-፣ ‹‹ጸሐይ በበጋ ወቅት ስድሰት ሰአት ላይ ከአናት ታዘንፋለች፣ የዐሰር ወቅት በግምት አስር ሰአት ተኩል ላይ ነው ብለን ብንገምት፣ የማቀዝቀዣው ሰአት ወደአስር ሰአት ገደማ ነው ማለት ነው፡፡›› አል-ሙምቲዕ ቅጽ ፡ 2 ገጽ ፡ 104፡፡
ማቀዝቀዙ በሕብረት ለሚስግዱም ሆነ ለብቻው ለሚሰግድ ሰው አጠቃላይ ነው፡፡ ሸይኻችን ኢብን ዑሠይሚን -አላህ ይዘንላቸው- ይህን መርጠዋል፡፡ በዚህ ሥር ሴቶችም ይጠቃለላሉ፡፡ ሴቶችም ሙቀቱ ብርቱ በሚሆንበት ወቅት ማቀዝቃዝ ነቢያዊ ፈለግ መከተል ተደርጎ ይቆጠርላቸዋል፡፡ ይህም አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ያስተላለፉት ሐዲሥ ሁሉንም የሚያጠቃልል ስለሆነ ነው፡፡